Logo

ታሪካዊ አመጣጥ





Chamber building

የደሴ ከተማ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የነጋዴ ማኅበራት ትልቁና አንጋፋው ማኅበር ነው፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ በአዋጅ ቁጥር 148/70 ሐምሌ 21 ቀን 1976 ዓ.ም የደሴ ከተማ የንግድ ም/ቤት በሚል ስያሜ ተመሥርቶ የቆየ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 341/1995 ዓ.ም እንደገና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋፋትና በማጠናከር የደሴ ከተማ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በሚል ስያሜ መተዳደሪያ ደንብ በመቅረጽ በከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አጸድቆ ምዝገባ አከናውኖ በይፋ ተመሠረተ፡፡
ም/ቤቱ ለትርፍ የማይሰራ ከፖለቲካ ነጻ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡ አሁን የደሴ ከተማ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት የአስተሳሰብ አድማሱን በማስፋትና ትኩረቱን ወደ ንግዱ ማኅበረሰብ በማዞር በግብር አከፋፈል፤ በንግድና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለንግዱ ማኅበረሰብ ተከታታይ ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መምህር በመቅጠር ያለ ትርፍ መሠረታዊ የኮምፒውተር ሥልጠና ለአካባቢው ወጣቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ስዓት ከ3300 በላይ ፈቃደኛ አባል ነጋዴዎችና አንድ የዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት በአባልነት አቅፎ የሚገኝ ሲሆን ፤ ከጠቅላላ ጉባኤ ቀጥሎ ም/ቤቱን በበላይነት የሚመሩ 11 የቦርድ አባላት አሉት፡፡ የቦርዱን ውሳኔ የሚፈጽምና የሚያስፈጽም አንድ ዋና ፀሐፊ አለው፡፡ 10 ቋሚና 10 ጊዜያዊ በድምሩ 20 የጽ/ቤት ሠራተኞች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል 6 ወንድ እና 14 ሴት በድምሩ 20 ናቸው፡፡ በሊዝ መነሻ ዋጋ ከከተማ አስተዳደሩ በወሰደው 445.95 ካ.ሜ ቦታ ላይ ደሴ ወሎ ባህል አምባ ፊት ለፊት B+G+6 ሁለገብ ህንጻ ገንብቶ ለጽ/ቤት አገልግሎት ከማዋሉም በላይ ሁሉንም የተጠናቀቁ ወለሎች በማከራየት ገቢ ማመንጨት ጀምሯል::